በኢትዮጵያ እና በግብፅ

በኢትዮጵያ እና በግብፅ መካከል ያለውን ታሪካዊ ግንኙነት የበለጠ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ገለፁ፣
==============================================================================
በግብፅ የኢፌዲሪ ልዩ መልዕከተኛና ባለሙሉስልጣን አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በኢትዮጵያና በግብፅ መካከል ያለውን ግንኙነት በተመለከተ በግብፅ ከሚገኘው አል አክባር ጋዜጣ ጋር እኤአ ጁለይ 30 ቀን 2019 ባደረጉት ቃለ ምልልስ በኢትዮጵያ እና በግብፅ መካከል ያለውን ታሪካዊ ግንኙነት የበለጠ ለማሰደግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ክቡር አምባሳደሩ በቃለ ምልልሳቸው በኢትዮጵያ እየተካሄደ ስላለው አጠቃላይ ሪፎርም፣ ሴቶችን ወደ አመራር ለማምጣት እየተደረገ ስላለው እንቅሰቃሴ፣ ስለ ታላቁ ህዳሴ ግድብ የደረሰበት ደረጃ፣ በሁለቱ አገሮች መካከል በጋራና በትብብር መስራት አስፈላጊነት በተመለከተ፣ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ማጠናከር በሚቻልበት ዙሪያ፣ ባለሀብቶች ኢንቨስት እንዲያደርጉ ማበረታትን በተመለከተ፣ ወቅቱን የጠበቀ የመሪዎች ጉብኝት ማድረግ አስፈላጊነት እና ሌሎች ተያየዥ ጉዳዮች ዙሪያ አል አክባር ጋዜጣ ጋር ቃለ መጠይቅ አድርገዋል።
ከመሪዎች ጉብኝት አንፃር ክቡር የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ባለፈው ጁን 2018 በግብፅ ያደረጉት ጉብኝት በሁለቱ አገሮች መካከል ያለው ግንኙነት መተማመን ደረጃ ላይ እንዲደርስ በማድረግ በአገራቱ መካከል ልዩ ግንኙነት እንዲፈጠር ማድረጉን አምባሳደር ዲና በቃለ ምልልሳቸው ገልጸዋል።  በተመሳሳይ ባለፈው ፌብሯሪ 2019 ክቡር ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ አል ሲሲ በአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ አዲስ አበባ በመጡበት ወቅት ከክቡር ጠቅላይ  ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ጋር ያደረጉት ውይይት የሁለቱን አገሮች ግንኙነት እንዲጠናከር ማድረጉን ገልወጸዋል፡፡ በሁለቱ አገሮች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ደረጃም ምክክሮች እየተካሄዱ መሆኑንና የግብፁ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ክቡር ሳሚህ ሹክሪ በቅርቡ ኢትዮጵያ በመገኘት  ከኢትዮጵያ አቻቸው ጋር ተገናኝተው ግንኙነቱን ማጠናከርና መተማመንን መፍጠር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መወያየታቸውን አምባሳደር ዲና አብራርተዋል። በተመሳሳይ  የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ክቡር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር አብይ አህመድ የተላከ መልክት ለግብፁ ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ አል ሲሲ ማድረሳቸውን አንስተዋል።
በአሁኑ ወቅት በሁለቱ አገሮች መካከል ያለው የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ትብብር በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ገልጸው፤ ነገር ግን ሁለቱ አገሮች ካላቸው ታሪካዊ ግንኙነት አኳያ ሲታይ ግንኙነቱ በሚፈለገው ደረጃ ላይ ስላልሆነ ከዚህ በላይ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ከአል አክባር ጋዜጣ ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ ገልጸዋል።
                                                                                                        ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
                                                                                       ቃል አቀባይ ጽ/ቤት
                                                                                                   ሐምሌ 25 ቀን 2011 ዓ.ም

Comments