የቀለም አብዩት ስልቶች

የቀለም አብዩት ሀይሎች የሚጠቀሙባቸው ስልቶች

1.  የቀለም አብዩቱን በምዕራፎች ከፋፍሎ በበቂ ዝግጅት መፈጸም

በአንድ አገር ላይ የቀለም አብዩት ለማካሄድ ሲፈልጉ በምዕራፎች ከፋፍለው በጥናት ላይ የተመሰረቱ የተለያዩ ተግባራትን ያከናውናሉ፡፡ የመጀመሪያው የቀለም አብዩት ኢላማ / target/ የሆነውን አገር የአመራር ሁኔታ፣ የመንግስትን ዓላማና አወቃቀር፣ የሚከተለውን ርዕዩተ አለምና የውጭ ድጋፍ ሁኔታውን እንዲሁም የአገሪቱን እድገት ሂደት፣ ሰብአዊና ተፈጥሯዊ ሁኔታዎችን በዝርዝር ያጠናሉ፡፡ በሁለተኛው ምዕራፍ በዝርዝር ጥናታቸው መሰረት በአገር ውስጥ እና በውጭ ለቀለም አብዩት ፍላጐታቸው መጠቀሚያ ሊሆኑ የሚችሉ አካላትና የህብረተሰብ ክፍሎችን ማግኘትና ሁኔታቸውን የመፈተሽና የማወቅ ሥራ ይሰራሉ፡፡

በሶስተኛው ምዕራፍ ለቀለም አብዩት ፍላጐታቸው መሳሪያ ለማድረግ የለዩዋቸው ተቋማት፣ የህብረተሰብ ክፍሎች ወይም ግለሰቦች ላይ በመቀራረብ ወይም ሰርገው በመግባት የማግባባት፣ የማሳመንና የማነሳሳት ተግባራትን ያከናውናሉ፡፡ በዚህ ሂደት አንዳንዶቹን በቀጥታ ጉዳዩን አውቀው እንዲገቡበት ሲያደርጉ አንዳንዶቹን ጉዳዩን በግልጽ ሳያውቁት በራሳቸው የግልና ቤተሰባዊ ህይወት ዙሪያ የሚያማልሉ ተስፋዎችን በማሳየት የአስተሳሰባቸው ሰለባ እንዲሆኑ ያደርጋሉ፣ በሂደትም ይጠቀሙባቸዋል፡፡ በአራተኛው ምዕራፍ የማግባባት፣ የማሳመንና የማነሳሳት ስራ የሰሩባቸውን አካላት የማደራጀት፣ በአስፈላጊው ሎጀስቲክ በመደገፍ አቅም እንዲፈጥሩ የማድረግ ስራ ይሰራሉ፡፡ ለአብነትም በኢትዩጵያ ውስጥ በ2007 ምርጫ ወቅት በተሞከረው የቀለም አብዩት ዞን 9 ጦማሪያን የሚል ስያሜ ያለው የኘሮፖጋንዳና ቅስቀሳ ቡድን እና የኢትዩጵያ ባለራዕይ ወጣቶች ማህበር የወጣቶች አደረጃጀት ፈጥረው ለመንቀሳቀስ ሞክረዋል፡፡


በአምስተኛው ምዕራፍ የግንባታ ስራ ይሰራሉ፡፡ የግንባታ ሥራው በአገር ውስጥና በውጭ ሊሰጥ ይችላል፡፡ በተለይም የውጭ እድል በመስጠት የሚካሄደው ግንባታ ለተሳታፊዎቹ የቁሳዊ ጥቅምና የተለየ አለም የማየት / Exposure/ ስለሚፈጥር ወደ አገር ውስጥ ሲመለሱ በቀላሉ ተከታዩችን የማፍራት አቅም ያገኛል፡፡ ለአብነትም በኢትዩጵያ የ2007 የቀለም አብዩት ሙከራ አዳዲስ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችን እንዲቋቋሙ በማድረግ አመራሮቹን የውጭ እድል በመስጠት የወደፊቱ የአፍሪካ ተስፋ ወጣት መሪዎች በሚል እንዲሸለሙ ያደረጉበት አጋጣሚ የዚህ አንዱ ማሳያ ነው፡፡ የግንባታ ስራው አዳዲስ ፓርቲዎችን በማደራጀት በህዝብ ዘንድ እንዲታወቁና ተቀባይነት እንዲያገኙ መስራት ብቻ ሳይሆን የቀለም አብዩት አጀንዳዎችና ጥያቄዎችን ለአብነትም የብሄራዊ እርቅ ጉባኤ ይጠራ፣ የፖለቲካ እስረኞች ይፈቱ፣ ወዘተ የሚሉትን ቀርፀው ያዘጋጃሉ፣ የተለያዩ የፖለቲካ ሀይሎችንም የማቀራረብና የጋራ አጀንዳ የመስጠት ተግባር ያከናውናሉ፡፡
በስድስተኛው ምዕራፍ በቀጥታ የአመጽና ሁከት ተግባሩን አፋፍሞ መቀጠል፣ ሽፋኑን ማስፋት፣ የቀለም አብዩቱን ለማሳካት የተዘጋጁትን ሁሉንም አቅሞችና ስልቶች በተቀናጀና በተጠና መንገድ ተግባራዊ ያደርጋሉ፡፡ በመጨረሻው ምዕራፍ መንግስት ተገዶ ወደ ድርድር የሚገባባቸውን አማራጨች በማቅረብ ወይም ሙሉ በሙሉ ከስልጣን እንዲለቅ በማድረግ የሽግግር መንግስት የማቋቋም ጉባኤ ያካሂዳሉ፡፡ የጉባኤው ፋይዳ የታይታና ህዝብን የማታለል ሲሆን በተጨባጭ ገና የቀለም አብዩቱ ሲታቀድ ለማስቀመጥ ያሰቧቸውን ቅጥረኞች ወደ ስልጣን በማምጣት አሻንጉሊት መንግስት አቋቁመው ስትራቴጂካዊ ጥቅሞቻቸውን ተግባራዊ ማድረግ ይጀምራሉ፡፡

2 የአመጽ ድባብ ማስፈን / Climate of protest መፍጠር/

የኒዩሊበራሊዝም ሀይሎች የቀለም አብዩት ታርጌት ባደረጉት አገርና መንግስት / Hostile state/ ተጨባጭ ሁኔታ በማጥናትና በመገምገም በመጀመሪያ የቀለም አብዩት ለማካሄድ ከሚያስቡበት ወቅት እስከ ሁለት አመት ቀደም ብለው በመጀመር በዋናነት መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች / NGOS/ በማህበራዊ ሚዲያዎች፣ አለም አቀፍ ተደራሽነት ባላቸው የቴሌቪዥንና የሬዲዩ ኘሮግራሞች እንዲሁም በህብረተሰቡ ውስጥ ቀስ በቀስ በሚፈጥሯቸው ትናንሽ አደረጃጀቶች በመጠቀም የኒዩሊበራሊዝም አስተሳሰብ ልዕልናን በህዝቡ ውስጥ የማስረጽና የማነሳሳት ሥራ ይሰራሉ፡፡ በሂደትም በህዝቡ ውስጥ የአመጽ ድባብ / Climate of protest/ እንዲፈጠርና እያደገ እንዲሄድ ያደርጋሉ፡፡ ለአብነትም የመንግስት ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎችን፣ ህጎችን የማጣጣል ህገወጥ ሰለፎችን የማድረግ፣ ወዘተ እንቅስቃሴዎችን ያደርጋሉ፡፡

3 አመጽና ሁከት አባባሽ የሆነ የሚዲያ ዘመቻ መክፈት

የቀለም አብዩት ሀይሎች ህግና ስርዓትን በመጣስ በሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች ላይ መንግስት ህግ የማስከበር እርምጃ ሲወስድ እርምጃውን ሽፋን በማድረግ የተጋነኑና ሀሰተኛ፣ ሆን ተብሎ የተቀነባበሩ ቪዲዩችን በማዘጋጀት በማህበራዊ ሚዲያዎች፣ ለቀለም አብዩት ተግባር ተብለው በተከፈቱ / OMN, ESAT , etc / እንዲተላለፋ ያደርጋሉ፡፡ ይህንን ሁኔታ በመጠቀም በየጊዜው እየጨመረ የሚሄድ ለአብነትም የተጎጂዎችን ምስል አሰቃቂ የሆነ ገጽታ በማላበስ ወደ አደባባይ ይዘው በመውጣት፣ መንግስትን፣ የተለያዩ የመንግስት አካላትንና ባለስልጣናትን በማብጠልጠል የተጠናከረ የሚዲያ ዘመቻ ይከፍታሉ፡፡

4 ተንኳሾችን፣ ተኳሾችንና ቅጥረኛ ወራሪዎችን መጠቀም

የቀለም አብዩት ሀይሎች በመጀመሪያውና በሁለተኛው ሂደት እንዳየነው የሚፈጥሯቸውን የአመጽና ሁከት ተግባራት ለማስቆም የፀጥታ ሀይሎች እርምጃ በሚወስዱበት ወቅት ጠንካራና ግንባር ቀደም የሆኑትን ኢላማ የሚያደርጉ ወይም ሆን ብለው ሰላምን ለማደፍረስ ትንኮሳ ለመፍጠር በህቡዕ ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ተንኳሾችና ተኳሾችን ያዘጋጃሉ፡፡ እነዚህ ተንኳሾችና ተኳሾች በሰላማዊ ሰልፈኛውና በፀጥታ ሀይሎች ላይ እርምጃ በመውሰድ ደም መፋሰስ እንዲፈጠር በማድረግ በአንድ በኩል የፀጥታ ሀይሎች የአመጽ ሀይሎችን ከመከላከል ተግባራቸው እንዲታቀቡ ለማድረግ ይሞክራሉ፡፡ በሌላ በኩል የፀጥታ ሀይሎች በበቀል ስሜት ተነሳስተው በሰላማዊ ሰዎች ላይ እርምጃ እንዲወስዱ ለማድረግና የጅምላ ጭፍጭፋ ተፈጸመ ብለው የሚዲያ ዘመቻ ለመክፈት እና አለም አቀፍ ማህበረሰብ በመንግስት ላይ ጫናውን እንዲያጠናክር ለአብነትም የኢኮኖሚ ማዕቀብ መጣል፣ ብድርና እርዳታ እንዳይገኝ ማድረግ፣ ወዘተ የመሳሰሉ የተጽዕኖ ተግባራትን ለመፈጸም ይንቀሳቀሳሉ፡፡
ሌላው መንግስት አመጽና ሁከቱን ለመቆጣጠር በሙሉ አቅሙ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ለማዳከምና የሀይል ሚዛኑን ለማናጋት በቅጥረኛ ሀይሎች በድንበር አካባቢ በቀጥታ ወረራ የሚፈጽሙበት ሁኔታም እንዳለ ማየት ይቻላል፡፡

5 የመንግስት ደጋፊዎችን ከህዝብ መነጠል

የመንግስት ደጋፊ ናቸው የሚሏቸውን ተቋማት፣ ድርጅቶችና ግለሰቦች ከህብረተሰቡ እንዲነጠሉና በሂደትም የአመጽና ሁከቱ ኢላማ እንዲሆኑ ያደርጋሉ፡፡ ለአብነትም በኢትዩጵያ ሁኔታ በ1997 ምርጫ ወቅት በተሞከረው የቀለም አብዩት የሞሃ ለስላሳ ምርት የሆኑ ለስላሳወችን ህዝቡ እንዳይጠቀም፣ በአሁኑ የ2008/9 የቀለም አአብዩት ሙከራም የሰላምና የስካይ ባስ መኪኖችን፣ ወዘተ ህዝቡ እንዳይጠቀም ለማድረግ እየለዩ ጥቃት እንዲደርስባቸው በማድረግ እንዲጠሉ ለማድረግ ሞክረዋል፡፡ ከዚህም በላይ በመሄድ የኢህአዴግ አባላትና ደጋፊዎች ከሆኑ ቤተሰቦችና ግለሰቦች ጋር የተለመዱ የሰው ልጆች የማህበራዊ ህይወት ግንኙነቶችን ለአብነትም ቢታመሙ አትጠይቋቸው፣ ቢሞቱ በቀብራቸው ላይ አትገኙ፣ እሳት አትጫጫሩ፣ ወዘተ እስከ ማለት የደረሰ ቅስቀሳ በማድረግ ደጋፊዎችን የመነጠልና የጥቃት ኢላማ እንዲሆኑ ለማድረግ ያልተሳካ ሙከራ አድርገዋል፡፡
የቀለም አብዩት ሀይሎች የራሳቸው አባል የነበረ ግለሰብ ወይም ቡድን በመካከል ላይ ድርጊታቸውን መቃወም ከጀመረ የመንግስት ወሬ አቀባይ፣ ከሀዲ፣በውስጣቸው የሚፈጠረውን ችግር ሁሉ እሱ እንደፈጠረው አድርገው፣ በዚህ ቀን ከዚህ የመንግስት ባለስልጣን ጋር አየነው፣ ወዘተ እያሉ መቆሚያ መቀመጫ እስከሚያጣ ድረስ የስም ማጥፋት ዘመቻ በመክፈት ከደጋፊዎች እንዲነጠል ያደርጋሉ፡፡ ለአብነትም በ1997 የቀለም አብዩት ሙከራ አቶ ልደቱ አያሌው የተባለ በወቅቱ የተደረገውን የቀለም አብዩት በተላላኪነት ለማስፈጸም የሞከረው የቅንጅት አመራር አባል ቅንጅት ወደ ፓርላማ መግባትና የአዲስ አበባ አስተዳደርን መረከብ አለበት በማለቱ ከደጋፊዎች እንዲነጠል ማድረግ ብቻ ሳይሆን በአገሪቱ ውስጥ እንደ አንድ ነፃ ሰው መንቀሳቀስ እንዳይችል እስከ ማድረግ የደረሰ ተግባር መፈጸማቸውን መጥቀስ ይቻላል፡፡

6 ሰበብ በመፍጠር አገርን ማውደም

የቀለም አብዩት ከፍላጎታቸው ውጭ ኢላማ በተደረገው አገር ለሚፈጠረው ሁኔታ ደንታ ስለሌላቸው የተለያየ ሰበብ ፈጥረው በቀጥታ በወታደራዊ ሀይል ጣልቃ በመግባት ወይም ተላላኪዎችን በመጠቀም አገርን የማውደም ተግባር ይፈጽማሉ፡፡ ለአብነትም በሶሪያና በየመን እየሆነ ያለው የዚህ አንዱ ማሳያ ነው፡፡ በኢትዩጵያ ሁኔታም በተለይም በ2008/9 የተሞከረው የቀለም አብዩት የፀረ ኢአትዩጵያ ሀይሎች ተላላኪ የሆኑት የሽብር ሀይሎች ህዝብ የሚጠቀምባቸውን የመሰረተ ልማትና የኢንሸስትመንት ተቋማት፣ የልማት ስራ ማሽነሪዎች፣ ፋብሪካዎች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት እንዲሰነዘር አድርገዋል፡፡ ይኼ ከየትኛውም ህዝብ ጥያቄ ጋር የሚገናኝና ፀረ ህዝብ ተግባር በቶሎ እንዲቆም ባይደረግ በሌሎች አገራትም እንደምናየው ግቡ አገርን ማፍረስና ማውደም ነው፡፡

7 ቅጥረኛ መንግስት በማቋቋም በማረጋጋትና መልሶ ግንባታ ስም አገርን መዝረፍ

የቀለም አብዩት ሀይሎች በአንድ አገር ላይ የጀመሩት የቀለም አብዩት ከተሳካና መንግስትን ማስወገድ ከተቻለ በኒዩሊበራሊዝም አስተሳሰብ ተቃኝተው የተማሩ ወይም ስብዕናቸው የውጭ ሀይሎችን ለሁሉም ነገር አድራጊና ፈጣሪ አድረገው የሚያዩ ግለሰቦችን በማሰባሰብ እንደፈለጉ የሚያሽከረክሩት አሻንጉሊት መንግስት ያቋቁማሉ፡፡ ለአብነትም በዩክሬን፣ በኢራቅ፣ ወዘተ የህዝባቸውን ጥቅም አሳልፈው ለኒዩሊበራሊዝም ሀይሎች የሚሰጡ አሻንጉሊት መንግስታት አቋቁመዋል፡፡ እነዚህ መንግስታት በአገሮቹ ውስጥ መረጋጋት ለመፍጠርና መልሶ ለመገንባት በሚል የአገሪቱን ሀብት በመልሶ ግንባታ ስም አሳልፈው ለእነዚሁ የኒዩሊበራሊዝም ሀይሎች የሚሰጡበት ሁኔታ ያመቻቻሉ ህዝቡን የበይ ተመልካች እንዲሆን ያደርጉታል፡፡

Comments